Numbers 21

የዓራድ መደምሰስ

1በኔጌብ ይኖር የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ እስራኤል በአታሪም መንገድ መምጣቱን በሰማ ጊዜ በእስራኤላውያን ላይ አደጋ ጥሎ ጥቂቶቹን ማረከ። 2በዚያን ጊዜ እስራኤል፣ “ይህን ሕዝብ አሳልፈህ በእጃችን ከሰጠኸን ከተሞቻቸውን ፈጽሞ እንደመስሳለን”
የዕብራይስጡ ትርጕም አንድን ነገር ወይም አንድን ሕዝብ ፈጽሞ በመደምሰስ፣ በማይሻር ውሳኔ ለእግዚአብሔር መስጠትን ያመለክታል።
ሲል ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ተሳለ።
3እግዚአብሔርም (ያህዌ) የእስራኤልን ልመና ሰምቶ ከነዓናውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰዎቹንና ከተሞቻቸውን ፈጽመው ደመሰሱ፤ ከዚህ የተነሣም ስፍራው ሖርማ
መደምሰስ ወይም ማጥፋት ማለት ነው።
ተባለ።

ከናስ የተሠራው እባብ

4እስራኤላውያን በኤዶም ዞረው ለመሄድ ስላሰቡ ከሖር ተራራ ተነሥተው ወደ ቀይ ባሕር
በዕብራይስጥ ያም ሱፍ ሲሆን፣ የደንገል ባሕር ማለት ነው።
በሚወስደው መንገድ ተጓዙ፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ በመንገድ ሳለ ትዕግሥቱ ዐለቀ፤
5በእግዚአብሔርና (ኤሎሂም) በሙሴም ላይ ተነሥተው፣ “በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብፅ ያወጣችሁን ለምንድን ነው? ምግብ የለ! ውሃ የለ! ይህን የማይረባ ምግብ ሰውነታችን ተጸይፎታል” ሲሉ ተናገሩ።

6በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) መርዘኛ እባቦች ሰደደባቸው፤ ሕዝቡን ነደፉ፤ ብዙ እስራኤላውያንም ሞቱ። 7ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥቶ፣ “በእግዚአብሔርና (ያህዌ) በአንተ ላይ በመናገራችን በድለናል፤ እባቦቹን ከእኛ እንዲያርቅልን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸልይልን” አለ፤ ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ።

8 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “እባብ ሠርተህ በዕንጨት ላይ ስቀለው፤ የተነደፈውም ሁሉ ወደ እርሱ በማየት ይድናል” አለው። 9ስለዚህ ሙሴ የናስ እባብ ሠርቶ በዕንጨት ላይ ሰቀለ፤ ከዚያም በእባብ የተነደፈ ማናቸውም ሰው ወደ ናሱ እባብ በተመለከተ ጊዜ ይድን ነበር።

ወደ ሞዓብ የተደረገው ጕዞ

10እስራኤላውያን ተጓዙ፤ በኦቦትም ሰፈሩ፤ 11ከዚያም ከኦቦት ተነሥተው፣ በፀሓይ መውጫ ትይዩ ባለው ምድረ በዳ በዒዮዓባሪም ሰፈሩ። 12ከዚያም ተጕዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ። 13ከዚያም ተነሥተው እስከ አሞራውያን ግዛት በሚዘልቀው ምድረ በዳ ባለው በአርኖን አጠገብ ሰፈሩ፤ አርኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል የሚገኝ የሞዓብ ወሰን ነው። 14እንግዲህ በእግዚአብሔር (ያህዌ) የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በዚሁ የተነሣ ነው፤

“…በሱፋ
የዕብራይስጡ ትርጕም አይታወቅም።
ውስጥ የሚገኘው ዋሄብ
አርኖንና
15ወደ ዔር የሚወስዱት
በሞዓብ ድንበርም የሚገኙት
የሸለቆች ተረተሮች።”
16ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ፣ “ሰዎቹን በአንድነት ሰብስባቸውና ውሃ እሰጣቸዋለሁ” ወዳለበት ብኤር ወደ ተባለው የውሃ ጕድጓድ ጕዟቸውን ቀጠሉ።

17ከዚያም እስራኤል ይህን መዝሙር ዘመረ፤

“አንተ ምንጭ ሆይ ፍለቅ!
እናንተም ዘምሩለት፤
18ልዑላን ለቈፈሩት፣
የሕዝብ አለቆች በበትረ መንግሥታቸውና በበትሮቻቸው ላጐደጐዱት፣
የውሃ ጕድጓድ ዘምሩለት።”
ከዚህ በኋላ ከምድረ በዳው ወደ መቴና ሄዱ፤
19ከመቴና ወደ ነሃሊኤል፣ ከነሃሊኤልም ወደ ባሞት፣ 20ከባሞትም ፈስጋ ላይ ሆኖ ምድረ በዳው ቍልቍል ወደሚታይበት በሞዓብ ወደሚገኘው ሸለቆ ተጓዙ።

የሴዎንና የዐግ ድል መሆን

21እስራኤል ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን እንዲህ የሚሉ መልእክተኞች ላከ፤

22“በአገርህ ዐልፈን እንድንሄድ ፍቀድልን፤ ወደ የትኛውም ዕርሻ ሆነ የወይን አትክልት አንገባም፤ ወይም ከየትኛውም ጕድጓድ ውሃ አንጠጣም። ከግዛትህ እስክንወጣ ድረስም የንጉሡን አውራ ጐዳና አንለቅም።”

23ሴዎን ግን እስራኤል በግዛቱ ውስጥ እንዲያልፍ አልፈቀደም፤ ሰራዊቱን በሙሉ አሰባስቦ እስራኤልን ለመውጋት ወደ ምድረ በዳው ወጣ፤ ያሀጽ እንደ ደረሰም ከእስራኤል ጋር ጦርነት ገጠመ። 24እስራኤል ግን በሰይፍ መታው፤ ከአርኖን እስከ ያቦቅ ድረስ ያለውንም ምድሩን ወሰደበት፤ ይሁን እንጂ የአሞናውያን ወሰን የተመሸገ ስለ ነበር ከያቦቅ አላለፈም። 25እስራኤልም ሐሴቦንና በአካባቢዋ ያሉትን መንደሮች ጨምሮ የአሞራውያንን ከተሞች በሙሉ በመያዝ እዚያው ተቀመጠ። 26ሐሴቦን የቀድሞውን የሞዓብን ንጉሥ ወግቶ እስከ አርኖን ድረስ ያለውን ምድሩን የወሰደበት የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተማ ነበረች።

27እንግዲህ ባለቅኔዎች እንደዚህ ያሉት ለዚህ ነው፤

“ወደ ሐሴቦን ኑ፣ እንደ ገና ትገንባ፤
የሴዎንም ከተማ ተመልሳ ትሠራ።

28“እሳት ከሐሴቦን ወጣ፤
ነበልባልም ከሴዎን ከተማ ተንቦገቦገ፤
የሞዓብን ዔር፣
በአርኖን ከፍታዎች የሚኖሩትንም በላ።
29ሞዓብ ሆይ፤ ወዮልህ!
የከሞስ ሕዝብ ሆይ፤ ተደመሰስህ!
ወንዶች ልጆቹን ለሽሽት፣
ሴቶች ልጆቹን ለምርኮ፣
ለአሞራውያን ንጉሥ ለሴዎን አሳልፎ ሰጥቷል።

30“እኛ ግን ገለበጥናቸው፤
ሐሴቦን እስከ ዴቦን ድረስ ተደመሰሰች፤
እስከ ኖፋ ድረስ ያሉትን፣
እስከ ሜድባ የተዘረጉትን እንዳሉ አፈራርሰናቸዋል።”
31ስለዚህም እስራኤል በአሞራውያን ምድር ተቀመጠ።

32ሙሴ ሰላዮችን ወደ ኢያዜር ከላከ በኋላ እስራኤላውያን በአካባቢዋ ያሉትን መንደሮች በመያዝ እዚያ የነበሩትን አሞራውያን አባረሯቸው። 33ከዚያም ተመልሰው ወደ ባሳን የሚወስደውን መንገድ በመያዝ ሄዱ፤ የባሳን ንጉሥ ዐግና መላ ሰራዊቱም ኤድራይ ላይ ጦርነት ሊገጥሟቸው ወጡ።

34 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “እርሱን ከመላው ሰራዊቱና ከምድሩ ጋር በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁና አትፍራው። በሐሴቦን ሆኖ ይገዛ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ላይ ያደረግህበትን ሁሉ በእርሱም ላይ አድርግበት” አለው።

35ስለዚህም እስራኤላውያን ዐግን ከልጆቹና ከመላው ሰራዊቱ ጋር አንድም ሳይቀሩ ሁሉንም ፈጇቸው፤ ምድሩንም ወረሱ።

Copyright information for AmhNASV